'፦ ምዕራፍ አሥር `፦
ለስምንት ወራት ያህል የዓለም ሕዝብ ዓይኖች ፋርስ ባሕረ‐ሰላጤ አካባቢ በሚከናወኑ ነገሮች ላይ አትኩረው ነበር። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሥራ ወደቤታቸው እንደተመለሱ የጦርነት ዜናን በቴልቪዥኖቻቸው ይከታተሉ ነበር። ለአጭር ጊዜ በዚህ ሁኔታ ትኩረታችን ተስቦ ነበር፤ ነገር ግን ማኅበረሰባችን እንዳለው እንደማንኛውም ሌላ ነገር ጦርነቱ ያሳሰበን ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው።
ከዚያ በኋላ መድፎች ጸጥ አሉ፤ የጦርነቱ ማብቃትም ይፋ ሆነና የዓለም ሕዝብ ትኩረቱን ወደሌላ አገሮችና ግጭቶች አዞረ። ስለሆነም በሌሎች አገሮች የሚከናወኑ ሁኔታዎች ከባግዳድ ይልቅ የዕለታዊ አበይት ርዕሰ ዜናዎች ሆኑ። ለመካከለኛው ምሥራቅ አዲስ የሰላም ዕቅድ ቀረበ፤ አዲሱ የዓለም ሥርዓትም የበላይነትን ያዘ።
ይሁን እንጂ ዓለም ጥቂት እፎይታ ባገኘበት ጊዜ ብዙ ሰዎች ፋርስ ባሕረ‐ሰላጤ ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮችን በቅርብ በመመርመር፥ ሁኔታዎቹን እግዚአብሔር ለአሁኒቱ ዓለም ባለው የእንቆቅልሽ ዕቅድ ውስጥ ሊያስማሟቸው ይሞክራሉ። ጦርነቱ ያስገኘው ጠቀሜታ ምንድነው? ሳዳም ሁሴን አሁንም ኢራቅን በመቆጣጠር ላይ ናቸው። የተባበሩት ኃይላትን ያቀናጁት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ከሥልጣን ሲወርዱ እሳቸው ግን በስፍራቸው ላይ ናቸው። ሳዳም ሁሴን በሥልጣን ላይ ለመቆየት መቻል ወይም አለመቻላቸው ገና አልለየለትም። ብዙዎች እኚህ ሰው በአጭር ጊዜ ይወገዳሉ የሚል ተስፋ የነበራቸው ቢሆንም እኚህ ሰው እስካሁን በስልጣን አሉ። ሰውዬው ፖለቲካዊ ለውጥ ለማድረግ በመሞከር ላይ ያሉም ይመስላሉ። የጥላቻ መንፈስ የሞላባቸው እኚህ ሰው የተሻሉ ሆነው ለመቅረብ ራሳቸውን ለጊዜው ሸሽገው ነበር። ከኩርዳውያን ተቃዋሚዎቻቸው ጋርም ሰላም ለመመሥረት ይሻሉ፤ ኩዌትን የወረሩ እኚህ አምባገነን ሰው ከዓረባውያን ወንድሞቻቸው ጋር የቅርብ ግንኙነትን በመፈለግ ላይ ናቸው። ራሳቸውን እንደናቡከደነፆር (ጥንታዊ የባቢሎን ንጉሥ) የቆጠሩት ሳዳም ዛሬ ለሕዝባቸው ስለሚበጅ ዲሞክራሲ በመምከር ላይ ናቸው።
የባሕረ‐ሰላጤው ጦርነት እንዳበቃ ሎስአንጀለስ (አሜሪካ) ውስጥ የሚታተም አንድ ጋዜጣ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ ሊቃውንት የሆኑ ስምንት ሰዎችን ሳዳም ሁሴን በፖለቲካ ሥልጣን ለመቆየት ስለሚኖራቸው ዕድል በተመለከተ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጠይቋቸው ነበር። ብዙዎቹ ሳዳም ሁሴን ረጅም ፖለቲካዊ ዕድሜ አይኖራቸውም ሲሉ፥ ራሚ ካውሪ የተባሉ፥ ደራሲና የፖለቲካ አምድ አዘጋጅ ፍልስጥኤማዊ ግን የሳዳም ሁሴንን በሥልጣን ላይ መቆየት አስመልክተው ቀጥሎ ያለውን ለየት ያለ አስተያየት ሰጡ።
"ሳዳም ሁሴን ምንም እንኳን ወታደራዊ ብልሀታቸው ዝቅተኛ ቢሆን፥ በሥልጣን የሚቆዩ ይመስላሉ...። በገሐድ ከሚታየው የጠላት የበላይነት አንጻር ያለውን የዓረቦችና የእስላሞች አይበገሬነት፥ እንዲሁም የድፍረት መንፈስ በግልጥ ተናገሩት፥ በግብርም ገለጡት። ይህ መንፈስ የተፈጠረው፦ (1ኛ) ዓረቦች ሰው‐ሠራሽ በሆነውና ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በተጀመረው አካባቢያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሥርዓት የተፈጠረው ቅያሜ፥ (2ኛ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዓለም ባጠቃላይ የጸጥታው ምክር ቤት ውሣኔን በመተግበር ጊዜ የሚያሳዩት አድልዎ፥ (3ኛ) ምዕራባውያን ቅኝና የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች የእነሱን ጥቅምና የሩቅ ዓላማ እንጂ፥ የአካባቢውን ዓረባዊ ሙስሊሞች ለማይጠቅም ዓላማ ወታደሮቻቸውን ወደመካከለኛው ምሥራቅ መላካቸው እና (4ኛ) እስራኤል ጎረቤቶቿ ከሆኑት ዓረቦች ይልቅ ብርቱ መሆን አለባት የሚለው የአሜሪካ ግትር አቋም እጅግ ቅር ባሰኛቸው ዓረቦች ዘንድ ስፍራ አግኝቷል።"
መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የተገኘው ድል አስደሳች ቢሆንም፥ ድሉ በዚያ አካባቢ ባለው ሁኔታ ላይ ያስከተለው ለውጥ ግን ጥቂት መሆኑን የዓለም ሕዝቦች አልተገነዘቡም። የትኛውም የመካከለኛው ምሥራቅ አገር መሪውን አልለወጠም። ሳዑዲት ዓረብና ኩዌት የሚተዳደሩት አሁንም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የመመሥረት ፍላጎት በሌላቸው ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ነው። ሶሪያና ኢራቅ ደግሞ ጊዜው ሲያመች የግዛት ድንበሮቻቸውን የማስፋፋት ምኞት ባላቸው የባዝ ፓርቲ አምባገነኖች ነው የሚተዳደሩት። ምዕራቡ ዓለም እጅጉን የነዳጅ ዘይት ጥገኛ ነው። ዓለም ከሚያስፈልጋት ነዳጅ ግማሹ የሚገኘው ደግሞ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ አንፃራዊ ሰላም አለ። ይሁን እንጂ ይህ ሰላም ዘላቂ ነው፥ ወይስ ቀጣዩ ማዕበል እስኪመጣ ድረስ የሚቆይ የእረፍት ጊዜ?
የመካከለኛው ምሥራቅ ችግር በ1970ዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ለመረዳት የነበረው ልዩ ትኩረትና ፍላጎት እንደገና እንዲያንሰራራ አድርጓል። ትንቢትን አስመልክተው የሚታተሙ መጻሕፍት ኒው ዮርክ ታይምስ በተባለው መጽሔት ላይ የላቀ ሽያጭ ያላቸው መጻሕፍት የሚለውን ስፍራ ሲይዙ፥ በክርስቲያን መጻሕፍት ሽያጭም አቻ የለሽ ሆነው ነበር። ብዙዎቹ መጻሕፍት መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት አንጻር መርምረዋል። የኔ ድርሰት የሆነውና "የባቢሎን ትንሣኤ" በሚል ርዕስ የሚታተመው መጽሐፍም ማንም ባልገመተው ሁኔታ ሽያጫቸው ከፍ ካሉት መጻሕፍት አንዱ ነበር።
አንድ ጓደኛዬ ሁልጊዜ፥ "ብርሃን ጥቃቅን ነፍሳትን" ይስባቸዋል የሚል አባባል አለው። ብዙ መጻሕፍት በአሁኑ ጊዜ የሚከናወኑ ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት አንጻር ሲተረጉሙ፥ ሌሎቹ ደግሞ ትንቢቶችን አሁን ካሉ ሁኔታዎች ጋር እንዲስማሙ እያደረጉ ሊያነቧቸው ሞክረዋል። ይህ የአተረጓጎም ልዩነት ረቀቅ ያለ ቢሆንም፥ ልዩነቱን መረዳቱ በጣም ጠቃሚ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ብርቱ አማኝ እንደመሆኔ፥ እግዚአብሔር ለዚህ ባቢሎንና እስራኤል ላሉበት ዓለም አንድ ዕቅድ ያለው መሆኑን ተረድቻለሁ። የትንቢቶቹ ፍጻሜ በተቃረቡ መጠንም፥ በዓለማችን የሚከናወኑ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ከተገለጡ ሁኔታዎች ጋር እጅግ ተመሳሳይ እየሆኑ እንደሚመጡ አምናለሁ። ይሁን እንጂ ለማንኛውም ንጽጽር መነሻ ሊሆን የሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ የወቅቱ ሁኔታዎች አይደሉም።
የፋርስ ባሕረ‐ሰላጤ ጦርነት በተከሰተ ጊዜ፥ የአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አስደናቂ "ትንበያዎች" ስሕተት መሆናቸው ተረጋገጠ። የበረሃው ማዕበል ዘመቻ የአርማጌዶን ውጊያ አልነበረም፥ ሳዳም ሁሴንም ሐሰተኛው ክርስቶስ አይደሉም፤ እንዲሁም ጦርነቱን ከፍጻሜ ያደርስ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ አልተመለሰም። ስከድ ሚሳይልና ተመሪ የሌዘር ቦምብ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ውስጥ ተገልጧል ያሉ ሰዎች፥ ፋርስ ባሕረ‐ሰላጤ ውስጥ የተደረገው ጦርነት ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 13 እና ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 50‐51 ውስጥ ባሉት ክፍሎች የተገለጠው የፍጻሜ ዘመን ጦርነት አለመሆኑን ተገነዘቡ። መጽሐፍ ቅዱስ ነበር የተሳሳተው? አይደለም። ችግሩ የእነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በተሣሣተ መንገድ መረዳታቸው ነበር። የወቅቱን ሁኔታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ከመመርመር ይልቅ፥ ሁኔታዎቹን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳሉ አድርገው ተመለከቷቸው።
የበረሃው ማዕበል ዘመቻ ቢያበቃም፥ የሚያዘናጉ ጥርጣሬዎች ግን አሉ። ጦርነቱ የአርማጌዶን ውጊያ ባይሆንም መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በቅርቡ በተከናወኑ ነገሮችና በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢቶች መካከል ያለው ተመሳሳይነት ችላ የሚባል አይደለም። እነዚህ መመሳሰሎች የታሪክ አጋጣሚዎች ወይስ ቀድሞ ስለዓለም ወደተወሰነው ፍጻሜ የሚያፋጥኑ ሁኔታዎች ናቸው? የእግዚአብሔር ቃል ስለባቢሎንና በታሪክ መድረክ ስለሚኖራት የመጨረሻ ዘመን ሚና ብዙ ይናገራል። በመሆኑም ወደፊት በዓለም ስለሚሆነው ነገር ለማወቅ የሚፈልግ ሰው የወቅቱን ሁኔታዎችና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትንቢት ሊያጠና ይገባል። ምክንያቱም ሁለቱ ነገሮች በመቀራረብ ላይ ናቸው።
ባቢሎን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ የጎላ ስፍራ አላት። በእግዚአብሔር ላይ የሚነሣ ሰብአዊ ኩራትና ዓመፅ ተምሳሌትም ናት። ባቢሎን የሚለውን ስም ያገኘችው ባብ (በር) እና ኤል (አምላክ) ከሚሉ ጥምር ቃላት ማለት ባቤል ከሚለው የእብራይስጥ ቃል ነው። ባቤል ሰው ራሱ ወደ እግዚአብሔር ለመግቢያ የሠራት በር ናት። ሰዎች ከእግዚአብሔር ዓላማ ውጭ በራሳቸው ጥረት ወደ እግዚአብሔር ለመድረሻ ተስፋ ያደረጉባትም ነበረች። (ዘፍጥ. 11)
ባቢሎን ያላትን ባህርይ እንደያዘች ነው በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምትጠቀሰው። እግዚአብሔር ላይ ያላት ጥላቻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው፥ ወታደሮቿ ኢየሩሳሌምን ባጠፉና ምድራዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ባፈራረሱ ጊዜ ነበር (586 ዓ.ዓ.)። ከዳዊት ቤት የሆነውን ንጉሥ ከዙፋኑ አውርደው በሰንሰለት በማሠር ወሰዱት። የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ አቃጥለው የይሁዳን ሕዝብ በምርኮ ወሰዱ። ዳንኤል ባቢሎንን "በአሕዛብ ዘመን" ማለት አሕዛብ ኃይሎች የእግዚአብሔር ሕዝብ ገዥዎች በሚሆኑበት ጊዜ የምትገኝ "የወርቅ ራስ" ይላታል።
ይሁን እንጂ፥ የባቢሎንን ድል የተነበየው እግዚአብሔር ራሱ ፍጻሜዋን አስከፊ መፈራረስ እንደሚያደርገውም ተስፋ ሰጥቷል። ነቢዩ ኢሳይያስ ውድቀቷን ሲገልጥ እንዲህ ብሏል፥ "እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደነበረው፥ የመንግሥታት ክብር የከላዳውያንም ትዕቢት ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች" (ኢሳ. 13፡19)። እጅግ ከፍ ከፍ ያለችው ከተማ ትንኮታኮታለች። የባቢሎን ውድቀት ከእስራኤል ትንሣኤ ጋር ባንድ ወቅት የሚከናወን መሆኑን ሲገልጥም እንዲህ ብሏል፥ "እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል" (14፡1)። እነዚህ የኢሳይያስ ትንቢቶች ገና አልተፈጸሙም።
ኢሳይያስ ባቢሎን ላይ ከተነበየ ከመቶ ዓመት በኋላ፥ ነቢዩ ኤርምያስም እንዲህ በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ተናግሯል፥ "ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ከተሞች እግዚአብሔር እንደገለበጣቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዲሁ ሰው በዚያ አይቀመጥም፥ የሰው ልጅ አይኖርባትም" (ኤር. 50፡40)። እግዚአብሔር ከባቢሎን ጥፋት በኋላ ሕዝቡን ወደ ምድራቸው የሚመልስ መሆኑንም ነቢዩ እንዲህ በማለት ገልጧል፥ "በዚያ ወራትም፥ በዚያም ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው ይመጣሉ። እያለቀሱም መንገዳቸውን ይሄዳሉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ይፈልጋሉ። ፊታቸውንም ወደዚያ አቅንተው፥ ኑ ከቶ በማይረሣ በዘላለም ቃል ኪዳን ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ፥ ብለው ስለጽዮን መንገድ ይጠይቃሉ" (50፡4‐5)።
አንዳንድ ምሁራን የባቢሎን ቂሮስ በተባለ የፋርስ ንጉሥ እና በሜዶ‐ፋርስ እጅ መውደቅ የኢሳይያስንና የኤርምያስን ትንቢት ፈጽመውታል ይላሉ። ይሁን እንጂ፥ እነዚህ ነቢያት ከተናገሯቸው ትንቢቶች ብዙዎቹ ያኔ አልተፈጸሙም። ከተማይቱ ቶሎ አልወደመችም፥ ቤቶችም አልተቃጠሉም። በነዋሪዎቿ ላይ የከፋ እልቂት አልደረሰም። የኢሳይያስንና የኤርምያስን ገለጣ በትክክለኛ ግንዛቤ ከተረዳነው፥ የቂሮስ ከተማይቱን መያዝ ትንቢታቸውን አልፈጸመውም። ታዲያ ይህ የጥፋት ትንቢት ከዚህ ቀደም ያልተፈጸመ ከሆነ፥ መቼ ነው ባቢሎን የምትጠፋው?
ሐዋርያው ዮሐንስ ያልተፈጸሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶችን ራእይ መጽሐፍ ውስጥ ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። ሐዋርያው፥ ባቢሎንን እግዚአብሔር ቃል ውስጥ በማስገባት አገሪቱ በታሪክና በትንቢት ውስጥ ያሏትን ሚናዎች ከሁለት ምዕራፎች በላይ በሆነ ክፍል በአንድ ላይ ገልጿቸዋል። ራእይ ከምዕራፍ 17‐18 ያለው ክፍል በዓለም ታሪክ ውስጥ የባቢሎንን ፍጻሜ ያመለክተናል። እስቲ በዮሐንስ ራዕይ የተዘረዘሩትን ትንቢቶች አካሄድ እንመልከት።
በራእይ ምዕራፍ 17 እና 18 መካከል ያለውን ግንኙነት መገንዘቡ፥ ምዕራፎቹ ውስጥ ባቢሎንን ለይቶ ለማወቅ ይረዳል። ብዙ ሰዎች እንደተረዱት ራእይ ምዕራፍ 17 እና 18 የተለያዩ ባቢሎኖችን ለየብቻ ይገልጣሉን? ይህን ጥያቄ በአዎንታ የሚመልሱ ሰዎች ራእይ 17 የሚገልጠው ሃይማኖታዊዋን ባቢሎንን ሲሆን፥ ምዕራፍ 18 ደግሞ ኢኮኖሚያዊቱን ባቢሎንን ማለት የፍጻሜ ዘመኑን የዓለም መሪ መዲና ነው ብለው ያምናሉ። ሌላው መረዳት ደግሞ ምዕራፎቹ ስለ አንዲት ባቢሎን ይገልጣሉን? ለዚህ ምላሽ አዎን ኢራቅ ውስጥ እንደገና ስለምትሠራው ባቢሎን የሚያመለክት ነው የሚል መረዳት ነው
ሐዋርያው ዮሐንስ ሁለቱም ምዕራፎች ውስጥ የጠቀሳቸውን ባቢሎኖች የገለጣቸው፥ በአእምሮው ውስጥ የነበረችው አንዲት ባቢሎን መሆኗን በሚያስገነዝብ ተመሳሳይ መንገድ ነው። ለምሳሌ፦
ባቢሎን
ስሟ አንድ ነው።
· "ታላቂቱ ባቢሎን" (ራእይ 17፡5)
· "ታላቂቱ ባቢሎን" (ራእይ 18፡2)
መለያዋ አንድ ነው።
· "ያየሃት ሴት...ታላቂቱ ከተማ ናት" (17፡18)
· "ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ወዮልሽ" (18፡10)
ልብሷ አንድ ነው።
· "ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቁዎችም ተሸልማ ነበር" (17፡4)
· "በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊ ልብስ ለተጎናጸፈች፥ በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት" (18፡16)
ሁለቱም ጽዋ ይዘዋል።
· "በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትም ርኩሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ያዘች" (17፡4)
· "በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት"(18፡6)
ከነገሥታት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ተመሳሳይ ነው።
· "የምድርም ነገሥታት ከርስዋ ጋር ሴሰኑ" (17፡2)
· "የምድር ነገሥታት ከርስዋ ጋር ሴሰኑ" (18፡3)
ከመንግሥታት ጋር ያላት ግንኙነት ተመሳሳይ ነው።
· "በምድር የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ" 17፡2)
· "አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ የተነሣ ወድቀዋል"(18፡3)
ከአማኞች ጋር የሚኖራት ግንኙነት ተመሳሳይ ነው።
· "ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት" (17፡6)
· "በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት" (18፡24)።
የማጥፊያው መሣሪያ ተመሳሳይ ነው።
· "ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል...በእሳትም ያቃጥሉአታል" (17፡16)።
· "በእሳትም ትቃጠላለች" (18፡8)
የጥፋቱ ምንጭ አንድ ነው።
· "እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ...በልባቸው አግብቶአልና"(17፡17)
· "እግዚአብሔር አመጻዋን አሰበ... የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና" (18፡5፥ 8)
ሁለቱም ምዕራፎች ውስጥ የተጠቀሰችው ባቢሎን ዝርዝር መመሳሰል ያስደንቃል። እያንዳንዱ ምዕራፍ ባቢሎን የተባለች ከተማን ይጠቅሳል። ሁለቱም ምዕራፎች ባቢሎንን የሚገልጧት ሀብቷንና ክፉ ቅርሷን ለይስሙላ የምታሳይ ከተማ እንደሆነች አድርገው ነው። ይህች ከተማ፥ የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ፍርድ እስክትቀበል ድረስ ከሌሎች መንግሥታት ጋር የምታደርገውን ሕገ ወጥ ግንኙነት ሁለቱም ምዕራፎች ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ዮሐንስ የሚገልጠው ስለሁለት ሳይሆን ስለአንዲት ከተማ ነው። በአእምሮው ያለችው አንዲት ባቢሎን ስትሆን፥ በዘመናት ሁሉ ራሷን በእብሪት ስታሰግግ የኖረችውም እሷው ናት።
ራእይ ምዕራፍ 17 እና 18ን ዮሐንስ ሲያቀርብ የምዕራፎቹን ስምምነት በሚያጎላና ሰፋ ባለ አቀራረብ ነው። ሁለቱን ምዕራፎች ያስገባቸው፥ ምዕራፍ 16፡19 ውስጥ እግዚአብሔር "በታላቂቱ ባቢሎን" ላይ ያወጀባትን የጥፋት ፍርድ በዝርዝር ለመግለጥ ነው፥ "ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች"። ይህን ነው ራእይ 17 እና 18 የሚያብራሩት።
ዮሐንስ ስለባቢሎን ውድቀት ከሰማይ የተሰጣትን ፍርድ ራእይ ምዕራፍ 19፡1‐3 ባለው ክፍል ውስጥ እንዲህ እያለ በአጭሩ ይገልጠዋል፥ "ሃሌሉያ" ይላሉ የሰማይ አእላፋት፥ ምክንያቱም "በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለፈረደባት" (19፡2)። ዮሐንስ ምዕራፍ 17 ውስጥ ደግሞ ባቢሎንን ጋለሞታ ብሎ ገልጧታል፥ ደግመውም፦ "ሃሌሉያ ጢስዋ ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል" ብሏል (19፡3)። "እስከ ዘላለም" የሚወጣው "ጭስ"፥ ምዕራፍ 18 ውስጥ የተገለጠችውን የተቃጠለችውን የባቢሎን ምስል ያመለክታል።
የምዕራፍ 16 እና 19 ጠቀሜታ የባቢሎንን ውድቀት ለማስተዋወቅና ታሪኩን ጠቅለል ማድረግ ነው። በዚህ ክፍል መሠረት በዮሐንስ አእምሮ ያለችው አንዲት ባቢሎን ስትሆን፥ እርሷንም ምዕራፍ 17 እና 18 ውስጥ በዝርዝር ገልጧታል። ባቢሎን ገናና ትሆናለች፥ እንደገናም ትወድቃለች።
ዮሐንስ ራእይ 17 ውስጥ ባቢሎን ላይ የተነገረውን ትንቢት የጀመረው ቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠችን ጋለሞታ በመግለጥ ነው። ለዚህ ታላቅ ጽሑፍ ዮሐንስ በቃላት የሚሣል ምሥሉን በመጀመሪያዎቹ ስድስት ቁጥሮች ገልጦታል። ከዚያ በኋላ ነው ቀጥሎ ባሉት አሥራ ሁለት ቁጥሮች ውስጥ የተጠቀሱትን ራእዮች ይገልጥ ዘንድ እግዚአብሔር አንድ መልአክ የሚልከው። ራእይ 17 ውስጥ የተጠቀሰው የእግዚአብሔር ዓላማ፥ ባቢሎን የምትጠፋበትን ምክንያት ለሐዋርያው ዮሐንስ መግለጥ ነው። ምዕራፍ 18 ደግሞ የባቢሎን ጥፋት በሚኖረው ውጤት ላይ ያተኩራል። እግዚአብሔር ባቢሎንን ለይቶ ለማወቂያ የሚረዱ አራት ቁልፍ የትርጉም መፍቻዎች በዚህ ሁለት ምዕራፎች ሰጥቶናል። ስለባቢሎን የሰጠን ትርጉም ወይም ፍች ራእይ 17፡1 ውስጥ የሚገኘው ሲሆን እርሱም፥ "በብዙ ውኃዎች ላይ የተቀመጠችው ታላቂቱ ጋለሞታ" ይላል። ባቢሎንን እንደጋለሞታ የሚገልጠው ቃል፥ ብዙዎች ባቢሎንን እንደ ሐሰተኛ የሃይማኖት ሥርዓት አድርገው እንዲረዱ ምክንያት ሆኗቸዋል። እግዚአብሔር ግን የባቢሎንን ሃይማኖታዊ ሁኔታ በመመልከት አይደለም ባቢሎንን እንደጋለሞታ ሴት የገለጣት። ጋለሞታ ያላት ለኢኮኖሚ ብልጥግና ስትል የምታሳየውን ከመልካም ስነምግባር የወጣ ምግባሯን አጉልቶ ለማሳየት ነው።
ራእይ 17 ውስጥ የተገለጠችው ክፉ ሴት፥ በብዙ ሁኔታዋ ትንቢተ ዘካርያስ ምዕራፍ 5 ውስጥ ከተጠቀሰችውና "ክፋት ከተሰኘችው ሴት ጋር ትመሳሰላለች። ዘካርያስ በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ እግዚእዘብሔር "ክፋት" ብሎ የሰየማትን ሴት ተመለከተ (ዘካ. 5፡7‐8)። ክፋት ሁሉ የሞላባት ነበረች። ዘካርያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ፥ የኢፍ መስፈሪያውን ሁለት መላእክት "በሰናኦር (ባቢሎን) ምድር፤ ቤት ይሠሩለት ዘንድ ይወስዱታል፤ በተዘጋጀም ጊዜ በዚያ በስፍራው ይኖራል አሉኝ" (ዘካ. 5፡11) ብሎ እንደነገረው ገልጧል። ክፋት በክፉ ሴት ተመስሎ አንድ ቀን ባቢሎን ውስጥ ይኖራል። ዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 17 ውስጥ የጠቀሳት ጋለሞታ የዘካርያስ ትንቢት ፍጻሜ ትሆን ይሆን?
ሌላው የእግዚአብሔር የትርጉም መፍቻ ቁልፍ፥ በጋለሞታይቱ ግንባር ላይ የተጻፈው ስም ነው፥ "ታላቂቱ ባቢሎን" ይልና "ምስጢር የሆነ ስም" "የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት" (ራእይ 17፡5) በማለት ሌሎች ስሞችንም ያክልበታል። የእነዚህ ስሞች ትርጉም ምንድነው?
ለጥያቄው መልስ ከመስጠታችን በፊት ሁለት ችግሮች መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል። አንደኛ፥ ሴቲቱ "ምስጢር" የተባለችው በምን ሁኔታ ነው? ዮሐንስ ሊነግረን የፈለገው፥ ሴቲቱ ግንባር ላይ የተጻፈው ቃል፥ "ምስጢር የሆንሽው ታላቂቱ ባቢሎን" የሚል ነው፤ ወይም "ታላቂቱ ባቢሎን" ተብሎ የተጻፈው ቃል ምስጢር ነው ለማለት ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው አማራጭ ከጽሑፉ አገባብ ጋር ይስማማል። ዮሐንስ መጽሐፉ ውስጥ ሌላ ስፍራ ሴቲቱን ሲጠቅሳት፥ "ታላቂቱ ባቢሎን" በማለት እንጂ "ምስጢር የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን" ብሎ አይደለም (ራእይ 16፡19 እና 18፡2ትን ይመልከቱ)።
መፍትሔ የሚሻው ሁለተኛ ችግር፥ የምስጢሩ ትክክለኛ ምንነት ነው። "ታላቂቱ ባቢሎን" የሚለው ስም ምስጢር የሆነው እንዴት ነው? አንዳንድ ሰዎች "ምስጢር" የሚለውን ቃል በመጠቀም፥ ባቢሎን የተምሳሌትነት ፍች እንዲኖራት ነው እግዚአብሔር የፈለገው ይላሉ። አዲስ ኪዳን ውስጥ ግን ምስጢር የሚለው ቃል የእውነትን ዓይነት ወይም ባህርይ ሳይሆን የሚያሳየው ተረድተውት ባልነበረ እውነትን መገኘትን ላይ የሚያተኩር ነው።
እግዚአብሔር ባቢሎንን ምስጢር ሲላት፥ በ"ጡብና ስሚንቶ" የተሠራች ከተማ እንጂ፥ የጥፋት ረቂቅ ኃይል ሥርዓት ናት ማለቱ አይደለም። ምስጢር ያላት፥ ይህን ለባቢሎን የተነገረ እውነት ቀደም ሲል ያልገለጠ መሆኑን ለማመልከት ነው። የእግዚአብሔር መልአክ ባቢሎን አውሬውን የምትጋልብ የመሆኗን ምስጢር ለዮሐንስ ከገለጠለት በኋላ፥ "የምትደነቅ ስለምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ...የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ" (17፡7) ይለዋል።
ለዮሐንስ የተገለጠለት ሁለቱ የዓለም ኃያላን (ጋለሞታይቱና የምትጋልበው አውሬ) በፍጻሜው ዘመን በሰላም አብረው የሚኖሩ የመሆኑን ምስጢር ነው። አራተኛው የዓለም ኃያል መሪ (አውሬው)፥ የሚነሣና የኢየሱስ መንግሥት በምድር ላይ በመመሥረቻው ዋዜማ ዓለምን የሚገዛ መሆኑን ነቢዩ ዳንኤል ተንብይዋል (ዳን. 2፡40‐45፤ 7፡23‐27፤ 9፡26‐27)። ሌሎች የብሉይ ኪዳን ነቢያት ግን፥ ባቢሎን በእግዚአብሔር ትንቢታዊ ዕቅድ መሠረት በኃያልነት ብቅ የምትል መሆኗን ነው የተነበዩት (ኢሳ. 13‐14፤ ኤር. 50‐51፤ ዘካ. 5፡5‐11)። ነገር ግን ሁለቱ ኃያላን በአንድ ወቅት ሊኖሩና እግዚአብሔር ለዓለም ባለው ዕቅድ ውስጥ ስፍራ ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነው? የዚህ ጥያቄ ምስጢር ነበር ለዮሐንስ የተገለጠለት።
እግዚአብሔር የሰጠው ሦስተኛ የትርጉም መፍቻ እግዚአብሔር ባቢሎንን የሚገልጥበት መለያ ስለሆነ ከሁሉ የላቀ ሳይሆን አይቀርም። ባቢሎን ስለተባለችው ጋለሞታ ብዙዎች የራሳቸውን ትርጉም ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ማንኛውም መለያ ወይም መግለጫ መጀመር የሚኖርበት እግዚአብሔር ራእይ 17፡18 ውስጥ ከገለጠው መለያ ነው። ምንባቡ ውስጥ መልአኩ ያቀረበው፥ እግዚአብሔር ስለጋለሞታይቱ የገለጠውን ነው። "ያየሃትም ሴት፥ በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት" ብሏል። እግዚአብሔር ስለጋለሞታይቱ የሰጠው ፍች ጠቃሚ የሚሆንበት ምክንያት፥ ራእይ 17 ውስጥ የተጠቀሰች ባቢሎንን እንደክርስትና ሃይማኖት መሪ ወይም አንዳች ምሥጢራዊ ሥርዓት ሳይሆን፥ እንደአንዲት ከተማ ስለሚገልጣት ነው። ባቢሎን ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ ያላት ከተማ መሆን አለባት። ምክንያቱም እግዚአብሔር "በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ" ብሎ ያውጅላታል። በዚህች የፍጻሜ ዘመን ባቢሎን ምንነት ላይ ምንም ታከለበት ምን፥ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሚገልጣት እንደ አንድ ከተማ ነው።
ዮሐንስ "የአውሬውን ውበት" ሲገልጥ፥ ሴቲቱ የምትቀመጥበት አውሬ ሰባት ራስ አለው ይለናል። የእግዚአብሔር መልአክ ይህን ጉዳይ ለዮሐንስ የገለጠለት እንዲህ በማለት ነው፥ "ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው። አምስቱ ወድቀዋል፥ አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል" (ራእይ 17፡9‐10)።
ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ምንድናቸው? ብዙዎች በተለምዶ ሰባቱ ተራራዎች የሚለው ቃል፥ በዮሐንስ ዘመን፥ ባለ ሰባት ተራራይቱ ከተማ በመባል የምትታወቀውን የሮም ከ